Statment of Faith

የእምነት መግለጫ !    Statement of faith

1. መጽሐፍ ቅዱስ
በብሉይና በአዲስ ኪዳን ያሉት ስድሳ ስድስቱም ቅዱሳት መጽሐፍት ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የጻፉት መሆኑን፣ በመጀመሪያው ጽሑፍ ምንም ስህተት የሌለበት፣ የቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ስርዓትና ምንጭ መለኪያ የሆነ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት ለአማኞችም ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናትና ለመምከር ሙሉ ኃይልና ስልጣን ያለው የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ እናምናለን። (2ኛ ጢሞ. 3፡16-17፤ 2ኛ ጴጥ. 1፡19-21፤ ኢያ.1፡8፤ 1ኛ ተሰ. 2፡13፤ 2ኛ ሳሙ. 23፡2፤ መዝ. (12) ፡6፤ ማቴ. 24፡24-35)።

2. እግዚአብሔር
በስማይና በምድር የሚገኙትን የሚታዪትን ፍጥረታት ሁሉ በፈጠረ ፍጹም፣ ህያው፣ ሁሉን ቻይ፣ ዘላለማዊ፣ የማይወሰን፣ የማይለወጥ፣ ሁሉን ዓዋቂ፣ ራሱን በማይከፈል ኑባሬ በሶስትነትና በአንድነት ይዞ በሚኖር አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በሆነው አንድ አምላክ እናምናለን። (ዘፍ. 3፡22፣ 17፡1፣ ዘዳ. 6፡4-5፣ መዝ. (132)፡7-12፣ ኢሳ. 40፡28፣ 48፡12-16፤ ሚል. 3፡6፤ዮሐ.17፡24)።

2.1 እግዚአብሔር አብ
እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለዓለም ኃጢያት በመስቀል ሞት መስዋዕት እንዲሆን የስጠ፣ ልጁንም በማመን አዳኝና ጌታ አድርገው ለሚቀበሉት ልጆቹ ይሆኑ ዘንድ ሰልጣን የሚሰጥና መንፈስ ቅዱስንም በወልድ ስም የላከ እንደሆነ እናምናለን። (ዘፍ. 3፡1-24፤ ዮሐ. 3፡16፣ 1፡12-13፤ ማቴ 5፡48፤ ኤፌ. 4፡6)።

2.2 እግዚአብሔር ወልድ
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ልጅ የሆነ፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ የተካከለ መለኮት፣ ከድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ የተፀነሰ፣ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ የሆነና ለዓለም ሁሉ ሐጢያት በቀራንዮ መስቀል ተሰቅሎ በመሞት እንደተቀበረ በሶስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሳና ባፈሰሰው ክቡር ደም ከእግዚአብሔር አብ ብቸኛ የመታረቂያ ምክንያት ሆኖ በዓርባኛው ቀን ወደ ሰማይ በማረግ በአባቱ ቀኝ የተቀመጠ፣ በሰማይ በዘላለማዊ ሊቀ ክህነት አገልግሎት በተሾመ፣ ስለ ሐጢያተኞች በሚማልድና በዓለም መጨረሻ በሙታንና በህያዋን ላይ ሊፈርድ ባለው፣ ዳግምኛ በሚመለሰው እናምናለን። (ዮሐ. 1፡1-5፤ ሉቃ. 1፡26-35፤ ቆላ. 2፡9፤ ዮሐ. 3፡14፤ ሮሜ. 5፡8-11፣ 6፡9፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡20-22፤ ሐዋ. 1፡1-9፣2፡32-36፤ ዕብ.
10፡12፣ 7፡15-25፤ 1ኛ ዮሐ. 2፡1፤ የሐዋ. 1፡10-11፤ ራዕ. 1፡6-7፤ ሉቃ. 10፡42-43)።

2.3 እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ
መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር በመለኮትነቱ እኩል የሆነ፣ የሚፈጥር የስላሴ ሶስተኛ አካል የአብና የወልድ መንፈስ የሆነ፣ የራሱ ስብዕና ያለው፣ የሚፈጥር ህይወትንም የሚሰጥ በነቢያት አድሮ ትንቢት ያናገረ በሐዋርያት ላይ የወረደ፣ ዓለምን ስለሐጢያት ስለጽድቅና ስለፍርድ በመውቀስ  ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን ሰዎች እንዲድኑ የሚረዳ፣ በአማኞች ውስጥ የሚያድር ያመኑትንም የሚያትም የሚመራና ኃይልንም የሚሰጥ እንዲሁም በመቀደስና የፀጋ ስጦታዎችን በማደል በቅዱሳን ህይወት እንደሚሰራ እናምናለን። (የሐዋ. 5፡3-4፤ ማቴ..28፡19-20፤ የሐዋ. 16፡7፤ ሮሜ 8፡9-10፤ ዘፍ. 1፡23፤ ኢዮ. 33፡4፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡10-12፤ ዮሐ. 15፡20፣ 6-27፣ 16፡7-15፤ ኤፌ.1፡14፤ 1ኛ ቆሮ. 12፡4-11)።

3. ሰው
ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሮ በሐጢያት ወድቆ ሙት በመሆን የጠፋ ሲሆን የሰውን ዘር ከኃጢያት ለማዳን በመስቀል ላይ ሞቶ በሶስተኛው ቀን ከሙታን በተነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በማመን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ዳግመኛ ተወልዶ የዘላለም ህይወት እንደሚያገኝ እናምናለን። (ዘፍ. 1፡26፣ 3-21፤ ሮሜ 5፡6-14፤ የሐዋ. 4፡12፤ ዮሐ. 3፡5-6፣14-18)።

4. ደህንነት
ሰው ከፈጣሪው ጋር ለመታረቅ፣ ከኃጢያትና ከዘላለም ኩነኔ ለመዳን የሚችለው ስለ ሰው ልጆች ኃጢያት በቀራኒዮ መስቀል ሞቶ በሶስተኛው ቀን ከሙታን በተነሳው በጌታችንና በመድሐኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ እንደሚሆን፣ ይህም ደህንነት ፍፁም ነፃ የሆነ የእግዚአብሔር የፀጋ ስጦታ መሆኑን፣ የወንጌልን የምስራች የሰሙትም በንስሐና በእምነት ክርስቶስ ኢየሱስን ሲቀበሎት በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ዳግመኛ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነው የዘላለም ህይወት እንደሚወርሱ እናምናለን። ቆላ. 1፡20፤ 1ጢሞ. 2፡5፤ ሮሜ 3፡20-26፣ 5፡6-11፤ ሮሜ 6፡23፤ ኤፌ.1፡3-14፣ 2፡8-9፤ ዕብ. 9፤25-28፤ ዮሐ. 1፡12-13፣3፡3-18፤ ቲቶ 3፡5-7)።

5. ቅዱስ ሥርዓቶች
ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ይጠብቁትና ያደርጉት ዘንድ በሰጣቸው ቅዱስ ስርዓቶች እናምናለን። እነርሱም፡

5.1 የውሃ ጥምቀት
የውሃ ጥምቀት ሰው ደህንነትን የሚያገኝበት ሥርዓት ሳይሆን በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው የዳኑ በግል ውሳኔያቸው የሚፈጽሙት እንደሆነና ይህም ጌታን በማመን ያገኙትን ደህንነት በሚታይ ሁኔታ ለመመስከር የሚፈጸም ሥርዓት እንደሆነ እናምናለን። (ማቴ. 28፡19፤ ሮሜ 6፡1-4፤ የሐዋ. 8፡36-39)።

5.2 የጌታ ዕራት
የጌታ ዕራት ሰው ደህንነትን የሚያገኝበት ሥርዓት ሳይሆን በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው የዳኑ በግል ውሳኔያቸው የሚፈጽሙት እንደሆነና ይህም ጌታን በማመን ያገኙትን ደህንነት በሚታይ ሁኔታ ለመመስከር የሚፈጸም ሥርዓት እንደሆነ እናምናለን። (ማቴ. 26፡17-30፤ ሮሜ 14፡12-25፤ የሐዋ. 22፡7-20፤ 1ቆሮ 11፡23-25)።

6.0 ጌታ ዳግመኛ ይመጣል
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ተመልሶ እንደሚመጣ በህያዋንና በሙታን ላይም እንደሚፈርድ እናምናለን። (ማቴ. 24፡27-42፤ የሐዋ 1፡10-11፤ ራዕይ 1፡7፤ ራዕይ 22፡12)።

Statement of faith in English